28/07/2026
በይርጋለም ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሚያሰራው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንጻ ግንባታ በከፍተኛ አመራሮች ተጎበኘ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ተዎድሮስ ምህረት እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አራት ኪሎ ባሻወልዴ ችሎት አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘውንና ከፊል ርክክብ የተደረገለትን የህንጻ ግንባታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በ #ይርጋለምኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር እየተገነባ የሚገኘው ባለ ሦስት ብሎክ የህንጻ ግንባታ ከፊል ርክክብ ተደርጎለት ስራ የጀመረ ሲሆን የቀሪዎቹን የሁለት ብሎኮች የግንባታ ስራ ለማጠናቀቅ በተሰራው ስራ ከ66 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑ በከፍተኛ አመራሩ ዕውቅና የተሰጠው ቢሆንም ከተያዘው ጊዜ አንጻር የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ አሁን ካለው በተሻለ ፍጥነት መጓዝ እንደሚገባ በአመራሮች መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
በአማካሪ መሀንዲሱና በህንጻ ተቋራጩ በኩል ስራውን በተባለው ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ በንዑስ ስራ ተቋራጮች አማካኝነት ስራውን ለማሰራት ጥረት እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ስራውን በተሻለ ፍጥነትና በጥራት ለማከናወን የሰው ኃይሉን ቁጥር ማሳደግና ማጠናከር እንዲሁም የፈረቃ ስራን ተጠቅሞ በተጨማሪ ሰዓት ስራውን በማሰራት ከወትሮው በተለየ አካሄድ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተገልጾላቸዋል፡፡
በመጨረሻም በአመራሮች በተሰጠ ቀጣይ አቅጣጫ ስራው ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የማካካሻ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የደረሰበት ደረጃ በየጊዜው በቅንጅት እንዲገመገምና ስራው አሁን በተያዘው ግለት በፍጥነትና በጥራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
Yirgalem Construction
በጋራ ኢትዮጵያን እንገነባለን!