31/05/2026
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ፣ አሁን Unilever ተብሎ የሚጠራው ታዋቂው የሊቨር ብራዘርስ ኩባንያ በአንድ ትልቅ የቴክኖሎጂ ችግር ተመትቶ ነበር።..
በፋብሪካቸው ውስጥ ሳሙናዎችን አሽጎ በካርቶን የሚለይ አውቶማቲክ ማሽን ነበራቸው። ነገር ግን ማሽኑ አልፎ አልፎ አንዳንድ ካርቶኖችን ሳሙና ሳይጨምርባቸው በባዶነታቸው አሽጎ ያሳልፍ ነበር።..
ባዶዎቹ የሳሙና ካርቶኖች ለገበያ ቀርበው ደንበኞች እጅ ሲገቡ ኩባንያው ከፍተኛ ቅሬታና የስም ማጥፋት አጋጠመው።
ይህንን ችግር ለመፍታት የፋብሪካው ከፍተኛ መሃንዲሶችና ሳይንቲስቶች ስብሰባ ተቀመጡ። ...
ችግሩን ለመፍታት ያቀረቡት መፍትሔ እጅግ ዘመናዊና ውድ የነበረ ሲሆን፣ ይኸውም በኤክስሬይ (X-ray) ጨረር የሚሠራ ትልቅ ማሽን መግጠም ነበር። ይህ ማሽን በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ እንዲህ ይሠራል።..
ካርቶኖቹ በኤክስሬይ ማሽኑ ውስጥ ያልፋሉ። ማሽኑ በውስጡ ሳሙና የሌለውን ባዶ ካርቶን ሲያገኝ የድምፅ ምልክት (Alarm) ያሰማል።..
ያኔ በፋብሪካው ውስጥ የሚሠራው ሰውዬ ማሽኑን አቁሞ ባዶውን ካርቶን በእጁ ያወጣል። ..
ኩባንያው ይህንን የኤክስሬይ ሲስተም ለመዘርጋትና ሰራተኞችን ለማሰልጠን በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር አውጥቶ ስራውን አጠናቀቀ። ማሽኑም በተሳካ ሁኔታ መስራት ጀመረ።..
ከጥቂት ወራት በኋላ ግን፣ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ የኤክስሬይ ማሽኑ የድምፅ ምልክት ማሰማቱን ሙሉ በሙሉ እንዳቆመ አስተዋለ። ማሽኑ ተበላሽቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ ማምረቻው ክፍል ወርዶ ሲመለከት ግን ያየው ነገር አስደነገጠው። የኤክስሬይ ማሽኑ አልተበላሸም፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል።...
ከማሽኑ ጥቂት ሜትሮች ቀደም ብሎ፣ በማጓጓዣው ቀበቶ (Conveyor Belt) አጠገብ፣ በፋብሪካው ውስጥ የሚሠራ አንድ ተራ የቀን ሰራተኛ አንድ ትልቅ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ማራገቢያ (Fan) አስቀምጦ ነበር!..
ሰራተኛው ማራገቢያውን የገጠመው በራሱ ተነሳሽነት ነበር። ማራገቢያው በከፍተኛ ኃይል ነፋስ ስለሚነፍስ፣ በውስጣቸው ሳሙና ያላቸው ከባድ ካርቶኖች ሳይነቃነቁ ቀጥ ብለው ያልፋሉ፤ ሳሙና የሌላቸው ባዶና ቀላል ካርቶኖች ግን በነፋሱ ኃይል ተገፍተው ከቀበቶው ላይ ወደ መሬት ይወድቃሉ።..
በዚህም ምክንያት ባዶዎቹ ካርቶኖች ወደ ኤክስሬዩ ማሽን ሳይደርሱ አስቀድመው ይወገዱ ነበር። ሰራተኛው ይህንን ለማድረግ ያወጣው ወጪ ጥቂት ዶላሮችን ብቻ ነበር።..
ከፍተኛ መሃንዲሶቹ ያተኮሩት “ባዶ ካርቶን ሲመጣ እንዴት ውስጡን አይተን ማሽኑን እናቆማለን?” በሚለው ውስብስብና ውድ ሳጥን ውስጥ ነበር። የፋብሪካው ተራ ሰራተኛ ግን ጥያቄውን ወደ ቀላሉ መንገድ ቀየረው።..
“ባዶ ካርቶን ሲመጣ በራሱ እንዲወድቅ እንዴት እናደርጋለን?”..
አንዳንድ ጊዜ ለትላልቅና ውስብስብ ችግሮች መፍትሔው የችግሩን ያህል ውስብስብ ሳይሆን፣ ነገሮችን በቀላሉና ከተለየ አቅጣጫ ማየት ነው።