19/10/2022
የዳሞት ወይዴ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት "አካታች ከተማ ለሀገራችን ብልፅግና "በሚል መሪ ቃል የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ
ዳሞት ወይዴ፣ጥቅምት 8/2015 ዓ/ም የዳሞት ወይዴ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት "አካታች ከተማ ለሀገራችን ብልፅግና "በሚል መሪ ቃል የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የዳሞት ወይዴ ወረዳ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አሰራት ወልደጊዮርጊስ እንደገለፁት በ2014 በጀት ዓመት ታቅዶ ያልተሠሩት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተስተዋሉ ደካማ ጎኖችን በመለየት ዕቅድ አካል በማድረግ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ መሰረተ ልማት ሥራዎች በመሳተፍ ከተማን ውብና ጽዱ የማድረግ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።
ለከተማችን ለውጥና ዕድገት የአመራሩና የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ አሥራት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰበዋል።
የዳሞት ወይዴ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን በየነ በበኩላቸው በ2014 በጀት ዓመት የታዩት ጉድለቶችን በማረምና በአዲሱ ዓመት የዕቅድ አካል በማድረግ ጽ/ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይሠራል ብለዋል።
አቶ ተስፋሁን አያይዘውም በ2015 በጀት ዓመት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ከባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅትና በቅርበት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በከተማችን የተጀመሩ መሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁና አዲስ ሥራ እንዲጀመር ትኩረት በመስጠት ከሚመለከተው አካላት ጋር በመናበብ ለአፈጻጸሙ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አቶ ተስፋሁን አስታውቋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የዳሞት ወይዴ ወረዳ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አሰራት ወልደጊዮርጊስና ፊት አመራሮች ፣የዳሞት ወይዴ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን በየነ፣የወረዳው አጠቃላይ አመራሮች ፣ የጽ/ቤቱ አጠቃላይ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ተገኝተዋል።