06/03/2026
ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም
ከ 26 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን የፊደል ገበታ አባት አርበኛው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ያረፉበት ዕለት ነበር።
‹‹ሀ ሁ…እውቀት ይስፋ…ድንቁርና ይጥፋ…ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ…›› ተስፋ ገብረ-ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ.....
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ፊደል ያላት አገር ናት፡፡ ይህም ከበርካታ የዓለም አገራት ተለይታ እንድትታይ ከሚያደርጓት መገለጫዎቿ መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፊደል በመላ አገሪቱ ተስፋፍቶ አገራዊ መገለጫነቱ ይዳብርና ብዙዎችም ማንበብና መፃፍ ችለው ከመሃይምነት ያመልጡ ዘንድ የአንድ ኢትዮጵያዊ ጠቢብ ርዕይና ጥረት ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ አርቆ አሳቢ ጠቢብ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ይባላሉ፡፡
ታህሣሥ 24 ቀን 1895 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ፣ ቡልጋ ውስጥ አክርሚት በተባለ ስፍራ በመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ወ/ሮ ሥዕለአብ ወ/ሚካኤል ቤት ይችን ዓለም የተቀላቀለው ልጅ ‹‹ተስፋ›› የሚል ስም ተሰጠው፡፡ 4 ዓመት ሲሞላውም ከአባቱ እግር ስር ተቀምጦ ፊደል መቁጠር ጀመረ፡፡
የሕፃኑ ተስፋ ወላጆች አራሽ ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች ስለነበሩ፣ ተስፋ እያደገ ሲሄድ ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ከብት ጥበቃው እንዲያተኩር ተደረገ፡፡ ተስፋ ከትምህርት ይልቅ ከብት ጥበቃ ላይ እንዲያተኩር መደረጉ ያልተዋጠላቸው የተስፋ አያት መሪጌታ ቢልልኝ ተስፋን እንዲያስተምሩላቸው መምህር ገ/አብ ለተባሉ የቤተክህነት ሊቅ ወስደው ሰጧቸው፡፡
መምህር ገብረአብም ሕፃኑን በደስታ ተቀብለው ንባብን ፣ ዳዊትን ፣ ውዳሴ ማርያምን ፣ መልክዓ ማርያምን ፣ መልክዓ ኢየሱስንና ሰዓታት ዘሌሊትን አስተምረው በድቁና አስመረቁት፡፡ ተስፋ ድቁናውን ከተቀበለ በኋላም በአክርሚት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ጀመረ፡፡
የተስፋ አባት መምህር ገብረሥላሴ ከቅስና ሙያቸውና ከግብርና ስራቸው በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው ከእፅዋት ቀለም እያነጠሩ ለፀሎትና ለአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጡ መጻሕፍትን በብራና ይፅፉና ያዘጋጁ ነበር፡፡ በጊዜው ግብር የሚከፈለው አዲስ አበባ ነበር፡፡ ግብር መክፈያ ወቅቱ ሲደርስና ነጋዴዎቹ እንደ ሚመጡ ሲያውቅ ፣ ነጋዴዎቹን ከኋላ ከኋላ እየተከተለ ፣ እነርሱ ሳያዩት ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ፡፡
ነጋዴዎቹ ብዙ ርቀት ከተጓዙ በኋላ ተስፋን አዩት፡፡ ወደኋላ እንዳይመልሱት ብቻውን ሊሆን ነው፡፡ ስለሆነም ይዘውት አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ለ 5 ቀናት ያህል ከነጋዴዎቹ ጋር በእግሩ ተጉዞ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ በወቅቱ ቤተመንግስት ውስጥ ሥራ ወደነበራቸው ወደ ታላቅ ወንድሙ ብርሃኔ ገ/ሥላሴ ዘንድ ቀረበ፡፡
ታላቅ ወንድሙ ሲያዩት ፣ ‹‹እንዴት መጣህ? ለመሆኑስ እናትና አባታችን ሰምተዋል?›› ብለው በጥያቄ ሲያፋጥጡት ተስፋ ‹‹አልተናገርኩም›› ይላል። ‹‹በል አሁን ገብተህ እረፍና አብረውህ ከመጡት ሰዎች ጋር ትመለሳለህ›› ብለው አስገቡት።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ትውልድ ስፍራው ሲመለስ ልቡም ዓይኑም ወደ ኋላ ዕየተመለከተ ፣ ‹‹እዚህማ ተመልሼ እመጣለሁ ፤ እስኪ የሚከለክለኝን አያለሁ›› እያለ እየዛተ ነበር፡፡ እንዳሰበውም አልቀረም በ 1909 ዓ.ም ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ሄደ፡፡
ታላቅ ወንድሙም ‹‹በል እንግዲህ ልብህ አላረፈም፤ መልሼም አልሰድህም፡፡ አንድ ክፍል ቤት አለችኝ ፤ እዚያች እረፍና የምትፈልገውን ትሰራለህ›› አሉት፡፡ ከተማውን ከተለማመደ በኋላም ተስፋ ራሱን ለመቻል ሲል ሱቅ በደረቴ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡ መርፌ ቁልፍ፣ ምላጭ ፣ መፋቂያና የመሳሰሉትን እያዞረ ይሸጥ ነበር፡፡ ከዚያም ታላቅ ወንድሙን ብድር ጠየቀ፡፡ የ75 ሳንቲም ብድር፡፡
በዚያች 75 ሳንቲም በወቅቱ ታዋቂ የነበረ ሽቶ ይሸጥ ነበር፡፡ ይህ ሽቶ ከፈረንሳይ በጅቡቲ በኩል አድርጎ ነበር የሚመጣው። ሽቶውን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስመጡ ነጋዴዎችም ነበሩ። ተስፋ ሽቶውን በ 75 ሳንቲም ገዝቶ ‹‹እሪ በከንቱ›› ወደሚባለው ሰፈር በመሄድ በሰፈሩ ላሉ ሴቶች በትርፍ ይሸጣል፡፡ ከዚህ ሽያጭ በሚያገኘው ገንዘብ መጽሐፍ ገዝቶ ይሸጥ ነበር፡፡ አዲስ አበባ በገባ በዓመቱ ፣ በወርሃ በየካቲት 1910 ዓ.ም ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ የሚያደርገውን ተግባር አከናወነ፡፡
የፊደል ገበታን አዘጋጀ፡፡ የተስፋ አባት መምህር ገብረሥላሴ ከእፅዋት ቀለም እያነጠሩ ለፀሎት እና ለአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጡ መጻሕፍትን በብራና ይፅፉና ያዘጋጁ ስለ ነበር ተስፋም የአባቱን ፈለግ ተከትሎ የፍየል ቆዳ በእንጨት ላይ በመወጠር እየፋቀ ፣ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፅዋት እያነጠረና ፊደላትን በመቃ ብዕር እየፃፈ በማራባት ወገኑን የሚጠቅም ስራ ያከናውን ጀመር፡፡
በዚያ ጊዜ ግዕዝም ሆነ አማርኛ ማንበብና መፃፍ ፣ በቤተ ክህነትና በቤተመንግስት የተገደበ እንጂ ሰፊው ህዝብ ዘንድ አልተዳረሰም ነበር፡፡ ስለዚህ ለሰዎች መፅሐፍ ቅዱስ በግዕዝም በአማርኛም ካነበበላቸው በኋላ ፣ ‹‹በሉ ግዙ፤ ይጠቅማችኋል›› ሲላቸው ፣ ‹‹አንተን አብረን ካልገዛን ማን ያነብልናል? ልጆቻችን አያውቁም ፤ እኛም አናነብም›› ይሉት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ‹‹እንዲህ ሰርቼ ፣ እንዲህ ቢማሩ ፣ በኋላ የተለያዩ መፅሀፎችን እያዘጋጀሁ እሸጣለሁ ፤ እኔም እጠቀማለሁ…›› ብሎ ሩቅ በማሰብ መጻሕፍትን ማዘጋጀት የጀመረው፡፡
በ 1921 ዓ.ም ማተሚያ ቤት በማቋቋም ‹‹እውቀት ይስፋ ፤ ድንቁር እና ይጥፋ ፤ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› የሚለውን ኃይለ ቃል አርዕስት በመስጠት ፊደልን ፣ ፊደለ ሐዋርያንና አቡጊዳን በሦስት ረድፎች እያዘጋጀ በማሳተም በመላ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመረ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከፊደላት ጋር ተዋወቁ፡፡
የእውቀት ብርሃንን በመላ አገሪቱ የማዳረስ ዓላማ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ሊሰናከል በተቃረበበት ጊዜ ተስፋ ራሱ ባዘጋጀው የፊደል ገበታ ተጠቅሞ አርበኝነቱን ጀመረ፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረሯ ጉዳይ እርግጠኛ እየሆነ በመጣበት ወቅት እንዲህ በማለት ጽፎ ለሕዝቡ አሰራጨ፡፡
‹‹ከባሕር እየወጣ መጣልን አሳው ፣
በሰይፍ እየመተርን ባረር እቆላን ፈጥነን እንብላው ፣
ጥንት አባቶቻችን ምግባቸው ይህ ነው ፣
ምነው ያሁን ልጆች ዝምታው ምንድን ነው ፣
የባሕሩ አሳ ወጥቶ ከጎሬው ፣
አጥማጁ አንቆ እንጂ ስጋውን ይብላው፡፡››
ተስፋ ይህን መሰል ወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎችን እያዘጋጁ በማተምና በማባዛት በመላ ኢትዮጵያ በማሰራጨት ሕዝቡ አገሩን ከወራሪው ኃይል ለመከላከል እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረር በጀመረችበት ወቅት አንዳንድ የኢትዮጵያን ባለስልጣናትን በገንዘብ እየደለለች የስለላና የማስከዳት ስራ ስትጀምር ተስፋ የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ፎቶ የጽሑፉ አርማ በማድረግ የዓድዋ ጀግኖች የፈፀሙትን አኩሪ ተግባር መድገም እንጂ ለገንዘብና ለስልጣን ብሎ አገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት እጅግ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ለመግለፅ:
‹‹የተረገመ ነው አገሩን የከዳ ፣
ክብሩን ነፃነቱን ሀበሻን የጎዳ፡፡
ከኢትዮጵያ (ከሀበሻ) ጠላት ጉቦ የበላችሁ ፣
የት ነው የምትበሉት አገር ሳይኖራችሁ፡፡
ያልታመኑ ሌቦች ከሹመት ተሸረው ፣
አገሪቱን ይምሩ ታማኞች ተመርጠው›› በማለት ስለሁኔታው ሃሳባቸውን በግጥም አቅርበው ነበር፡፡
ተስፋ እነዚህንና መሰል ጽሑፎችን እያተመ በብዛት ሲያሰራጭ አገር በመክዳት የተጠረጠሩት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆኑ ወረራውን የሚቃወሙትና የከዳተኞቹን ድርጊት የሚያወግዙት ሹማምንት ጭምር ያጉረመርሙ ጀመር፡፡ በጊዜው ይታተሙ የነበሩ ጽሑፎች ሁሉ በጽሕፈት ሚኒስቴር ሳይመረመሩና ፈቃድ ሳይሰጣቸው ማሰራጨት የተከለከለ ስለነበር ተስፋ ተይዞ እንዲቀርብና በየክፍላተ አገሩ አሳትሞ ያሰራጫቸው ጽሑፎችም እንዲሰበሰቡ ታዘዘ፡፡
ተስፋም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ፊት ቀርቦ ‹‹በመላ ኢትዮጵያ ያሰራጨኸውን ስብከት የት ነው ያሳተምከው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡ እርሱም ‹‹በሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ ግቢ ውስጥ ባለው ማተሚያ ቤት ነው›› ብሎ መለሰ፡፡ በዚህም ምክንያት ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ስለምን በብፁዕነትዎ ግቢ ውስጥ ወንጀል ተሰራ?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አገራችሁን አትካዱ ፤ ከጠላት ጉቦ አትቀበሉ› ብሎ መስበኩ ወንጀልነቱ ምንድን ነው?…›› ብለው መልስ ሰጡ፡፡ ጉዳዩ እንዲጣራ ተወስኖ ተስፋ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ፡፡ ወዲያውኑም የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ እየገፋ በመምጣቱ ያለመንግሥት ፈቃድ እንዲህ ዓይነት ጽሑፎችን እንዳያትምና እንዳያሰራጭ ዋስ ጠርቶ ከእስር ተፈታ፡፡
ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅትም ተስፋ ሕዝቡ ለነፃነቱ እንዲታገል የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን እያሳተሙ ከማሰራጨት አልቦዘነም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ባለው መሳሪያ ጠላትን እንዲከላከልና እጁን አጣጥፎ እንዳይቀመጥ የሚያሳስብና ‹‹የኢትዮጵያ ፋና›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ እያሳተመ ያሰራጭ ነበር፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ተስፋ ታሰረ፡፡ በመኖሪያ ቤቱ የነበሩትን ጽሑፎች ቀደም ብሎ በመደበቁ በፋሺስቶች ዘንድ እንደወንጀለኛ የሚያስቆጥረው ነገር ስላልተገኘበት ከእስር ተፈታ፡፡ ከእስር ከተፈታ በኋላም ጽሑፎችን በማተምና በማሰራጨት አርበኞችን የማነቃቃት ስራውን ቀጠለበት፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት (1928 ዓ.ም - 1933 ዓ.ም) ብዙዎች በዱር በገደል ሆነው ወራሪውን ኃይል ፋታ ነስተው ታላቅ የአርበኝነት ተጋድሎ ባደረጉበት ወቅት ፣ ተስፋ ገብረሥላሴ የተለያዩ ወረቀቶችን እያባዛ የአገር ፍቅር ስሜትን የሚኮረኩር ፤ የአርበኞችን ጀግንነትም የሚገልጹ ጽሑፎችን በከተማ ይበትን ነበር፡፡
ተስፋ በመልዕክቶቹ አርበኛው እንዳይበተንና ኅብረቱን አጠንክሮ እንዲፋለም ከማሳሰብ ባሻገር የአርበኞች ማኅበር እንዲቋቋም ሃሳብ ካቀረቡ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ምክረ ሃሳብ መሰረትም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በ 1931 ዓ.ም ሊቋቋም ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፋሺስት ኢጣሊያ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይፈፅም የነበረውን ግፍና በደል በወቅቱ ለንደን ይገኙ ለነበሩት ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ደብዳቤ በመላክ ያሳውቁ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ተስፋ በድጋሜ በፋሺስት ወታደሮች ታሰረ፡፡ ማተሚያ ቤቱም ተወረሰበት፡፡ በእስር ቤቱ ውስጥም እስረኞች በረሀብና በውሃ ጥም መጎዳታቸውን ተመለከተ፡፡ የእስር ቤቱን ኃላፊ አስጠርቶ ‹‹… አርባ ማር ትሬዛ ብር ስላለኝ ይፈቀድልኝና ዳቦ ገዝቼ ላብላቸው…›› ብሎ ጠየቀ፡፡ የእስር ቤቱ ኃላፊም በተስፋ አነጋገር ስሜቱ በመነካቱ ብዙ ዳቦ ፣ ሻይና ውሃ መጥቶ ለእስረኞች እንዲታደላቸው በማድረጉ እስረኛውን ሁሉ በረሀብና በውሃ ጥም ከማለቅ ታደገው፡፡
ከወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ኃይል መባረር በኋላ ተስፋ ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ማተሚያ ቤቱንም በአዲስ መልኩ በማጠናከር ‹‹ሀ ሁ… እውቀት ይስፋ …ድንቁርና ይጥፋ… ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ.. ›› ብለው ጽሑፎችን ማሳተም እና ማሰራጨት ቀጠሉ፡፡ በዚህ ስራቸውም ትምህርትን በመላ ኢትዮጵያ ለማዳረስና መሃይምነትን ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ ዘመናዊ የሕትመት መሳሪያዎችን ከውጭ በማስመጣት ስራቸውን አስፋፉ፡፡
‹‹ሀ ሁ››ን ፣ ‹‹አቡጊዳ››ንና ‹‹መልዕክተ ዮሐንስ››ን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ 300 በላይ መፅሐፍትን ማዘጋጀትና ማሳተም ችለዋል፡፡ የፊደል ገበታን ቀርፀው መሃይምነትን ለማጥፋት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በአርበኝነት ትግላቸው ላደረጉት ተጋድሎ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ለስራ እጅግ የተለየ ክብር ነበራቸው፡፡ 97ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ‹‹ … ሆዴ እህል በልቶ ቢጠግብም እጄን ስራ ይርበዋል …›› በማለት ለስራ ያላቸውን ጉጉትና አክብሮት ገልፀው ነበር፡፡ እድሜያቸው ገፍቶ እንኳ በድርጅታቸው ዋና መስሪያ ቤት እየተገኙ የስራውን ሂደት ይቆጣጠሩና እርሳቸውም ኃላፊነታቸውን ይወጡ ነበር፡፡
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከእፅዋት የቀለም ዱቄት ቀምመውና በጥብጠው ፣ ከመቃ እንጨት ብዕር ቀርጸው በወረቀት ላይ ፊደል በመፃፍ በካርቶን ላይ እየለጠፉ በማቅረብ ሚሊዮኖችን ከመሃይምነት ያወጡና የእውቀትን ብርሃን የፈነጠቁ ታላቅ የአገር ባለውለታ ናቸው፡፡
‹‹ያነበበ እውቀትን ጠገበ ፣
ድንቁርናን ክዶ ወደ እውቀት ተሳበ ፣
የጥበብን ገጿን ለማየት ቀረበ›› የሚለው ግጥም ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴን የሚመለከት ይመስላል፡፡
ቀኛዝማች ተስፋ የስራቸውን አስፈላጊነትና የትምህርትን ጥቅም ሲያስረዱ ‹‹ማንኛውም ሰው እናት አገሩ ባስገኘችለት፤ ሊቃውንት አባቶች አዘጋጅተው ባቆዩለት ፊደል ተምሮ ማንበብና መፃፍ ተቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል፡፡ መምህራንም የፊደላትን ስነ ባሕርይ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም በየጊዜው የሚነሳው ብሔራዊ ትውልድ ራሱን ክዶ ሌላውን ሆኖ እንዳይገኝ ወይም ‹መነሻውን አያውቅ መድረሻውን ይናፍቅ› ከመሰኘት ነፃ ያደርገዋል›› ብለው ነበር፡፡
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ በስራቸው ላይ ከጎናቸው ሆነው ሲያበረታቷቸውና ሲደግፏቸው ከኖሩት ወይዘሮ አለሚቱ ንጉሤ ጋር ጋብቻ መስርተው 13 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ በሕይወት እስከ ነበሩበት ጊዜ ድረስ 42 የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል፡፡
‹‹ሀ ሁ … እውቀት ይስፋ… ድንቁርና ይጥፋ … ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ...›› ብለው በማወጅ ድንቁርናን ለማፋት በመላ ኢትዮጵያ የፊደል ሰራዊትን ሲያዘምቱ የኖሩት አርበኛው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በማግሥቱ ግንቦት 27 ቀን 1992 ዓ.ም በቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
“እውቀት ይስፋ ፣ ድንቁርና ይጥፋ
ይህ ነው ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ።"