01/04/2026
!
፡ መንግሥት በነዳጅ አቅርቦት ላይ አዳዲስና ጠንከር ያሉ ውሳኔዎችን አስተላለፈ::
አዲስ አበባ - መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ቀውስ እና የዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ መናጋትን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቅርቦት እጥረቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተከታታይ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል::
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከጦርነቱ በፊት 80 ዶላር የነበረው የአንድ በርሜል ነጭ ናፍጣ ዋጋ በአሁኑ ወቅት ወደ 230 ዶላር አሻቅቧል። በተመሳሳይ ቤንዚን ከ70 ወደ 150 ዶላር ደርሷል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራት የነዳጅ ግዥ ውል በአቅራቢ አገራት ምክንያት በመስተጓጎሉ፣ 180 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ሳይቀር መቅረቱን ጠቁመዋል።
ይህም የናፍጣ የቀን አቅርቦት ከ9.2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር እንዲቀንስ አድርጎታል።
የተፈጠረውን እጥረት በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የቅድሚያ አሰጣጥ ሥርዓት ዘርግቷል። በዚህም መሠረት ነዳጅ በቅድሚያ የሚያገኙት፦
1. ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች (ለስርጭት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል)
2. ከፍተኛ አምራችና ላኪ ድርጅቶች (በቀጥታ እንዲያገኙ ይደረጋል)
3. መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች
4.ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮችና ማሽነሪዎች
5. የብዙኃን ትራንስፖርት (አውቶቡሶችና በናፍጣ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻዎች)
ሁኔታውን 24/7 የሚከታተል "ልዩ ኦፕሬሽን ክፍል" በማዕከል ደረጃ ተቋቁሟል። እስካሁን በተደረገ ክትትል በሕገ-ወጥ ተግባር የተሳተፉ 658 ግለሰቦች (የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ) በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ 720 ሺህ ሊትር ነዳጅ ተይዞ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል።
ምንም እንኳን የዓለም ዋጋ በሦስት እጥፍ ቢጨምርም፣ መንግሥት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር፣ በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል። እስካሁን በአጠቃላይ 262 ቢሊዮን ብር ለድጎማ ወጪ ተደርጓል።
ሚኒስትሩ ወቅታዊውን ችግር በጋራ ለመሻገር ዜጎች የሚከተሉትን ተግባራት እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፦
1. ነዳጅን በከፍተኛ ቁጠባ መጠቀም።
2. የአጭር ርቀት ጉዞዎችን በእግር የመጓዝ ባህልን ማዳበር።
3. አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝ።
4. በነዳጅ ግብይት ላይ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለሚመለከተው አካል ማጋለጥ።
Via ENA
Pic. ጉርሻ page