11/06/2026
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ የከብተሌ ከተማ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታን በ400 ሚሊዮን ብር ለማከናወን የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈረመ።
የዓመታት የወረዳው ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የነበረውን የከተማዋን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር የሚፈታው ፕሮጀክቱ የሚገነባው በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ እና በዩኒሴፍ የ400 ሚሊዮን ብር የመቀናጆ በጀት ትብብር ነው።
ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን የውል ስምምነት የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በአሰሪነት፣ ጢስ እሳት የውኃ ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደግሞ በተቋራጭነት ውሉን ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የቢሮው ያልተጓደለ ድጋፍና ክትትል እንዳለ ሆኖ የዞኑና የወረዳው አስተዳደር እና የተጠቃሚው ህብረተሰብ ድጋፍና ከፍተኛ ሚና እንዳለው በውል ስምምነቱ መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።