22/05/2021
የኮስሞስ ሳዱካ አባት በአራት አመቱ ነበር የሞተበት፡፡ ድሮውንም የተወላዳ ኑሮ ስላልነበራቸው የአባትየው መሞት ችግር ውስጥ ጣላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በአራት አመቱ ከወንድሙ ጋር መንገድ ላይ ምግብ እያዞሩ መሸጥ ጀመሩ፡፡ ናይጄሪያ ውስጥ ለመክሰስ የሚሸጠውን እና ከባቄላ የሚሰራውን አካራ እየዞረ ሲሸጥ ጎበዝ ሴልስ መሆኑ ያስታውቅ ነበር ይባልለታል፡፡
እድሜው ሰባት አመት ሲደርስ በኢግባ አዲቦ ሲስተም ለስራ ሃብታም አጎቱ ጋር ተላከ፡፡ በናይጄሪያ ኢግባ አዲቦ ሲስተም የሚባል ባህላዊ አሰራር አለ፡፡ አንድ ሰው ከተወለደበት ገጠር ወጥቶ ወደ ከተማ ይሄዳል፡፡ ከዛ ቢዝነስ ተሳክቶለት ጥሩ ስራ መስራት ሲጀመር ወደ አደገበት ገጠር ተመልሶ ወጣት ልጆችን ወደ ከተማ ይዞ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ልጆች ከሰውየው ጋር እየሰሩ ከሰባት እስከ ስምንት አመታት ይቀመጣሉ፡፡ ይሄ ቢዝነስ እንዴት እንደሚሰራ እንዲማሩ ይጠቅማቸዋል፡፡ በመቀጠልም ቢዝነስ ለመጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ ባለ ሃብቱ ይሰጣቸው እና የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ ይረዳቸዋል፡፡
በዚሁ ሲስተም መሰረት ኮስሞስ ወደ አጎቱ የሞተር ሳይክል መለዋወጫ እቃዎች የመሸጥ ቢዝነስ ተቀላቀለ፡፡ ምግቡን አጎቱ የሚያቀርበለት ሲሆን ማታ ማታ ደግሞ በሱቁ ውስጥ ፍራሽ አንጥፎ ሱቁን እየጠበቀ ያድራል፡፡ በዚህ ሲስተም ልጆቹ መጨረሻ ላይ ለቢዝነስ መጀመሪያ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ሌላ በየወሩ ደሞዝ አይከፈላቸውም፡፡ አጎቱን ሰባት አመት ካገለገለ በሆዋላ ከአጎቱ ጋር አለመግባባት ውስጥ መግባት ጀመሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ላገለገለበት የናይጄሪያን 200 ናይራ ሰጥቶ ከስራ አሰናበተው፡፡ በጊዜው 200 ናይራ ማለት አንድ ዶላር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ኮስሞስ ለአጎቱ “ሰባት አመት አገልግዬ የሚገባኝ ይሄ አይደለም፡፡ የዛሬ አምስት አመት እንገኛኝ፡፡ ያረከኝ ነገር ይፀፅትሃል” ብሎ ተናገረው፡፡
መጀመሪያ ከወንድሙ ጋር ሆነው የመለዋወጫ ሱቅ ከፈቱ፡፡ ከወንድሙ ጋር በብር አያያዝ መስማማት ስላልቻሉ ሱቁ ተዘጋ፡፡ በመቀጠል ከጓደኛው ጋር ሆነው ኮስዴቭ የተባለ የሞተር ሳይክል መለዋወጫ እቃዎች ሱቅ ከፈቱ፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ግን ከስረው ሱቁ ተዘጋ፡፡ በሶስተኛ ዙር ከሚስቱ ከቻሪቲ ጋር በመሆን ኮስቼር ሞተርስ የተባለ የመለዋወጫ እቃዎች ሱቅን በ300 ናይራ ከፈተ፡፡ “ነጋዴ ስትሆን እቃን እንዴት መሸጥ እንዳለብህ ብቻ ሳይሆን እቃን ከየት ገዝተህ ማምጣት እንዳለብህ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ እኛ ስራውን ስንጀምር ብር ስላልነበረን በዱቤ እቃ የሚሰጡንን አካፋፋዮች ደጅ መጥናት ነበረብኝ፡፡ የቤት ኪራይን እና ሌላም ሌላም ወጪ በዱቤ ለማግኘት ወይም ዋጋ ለማስቀነስ መሟሟት ነበረብኝ” ብሏል፡፡
በ1982 አ.ም የናይጄሪያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የመለዋወጫ አስመጪነት ፈቃድን ለአስር የግለሰብ ድርጅቶች ሰጠ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ኮስቼር ሞተርስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ኮስሞስ ከጃፓን የመኪና እና የሞትር ሳይክል መለዋወጫዎችን እያስመጣ በናይጄሪያ ማከፋፈል ጀመረ፡፡
ዛሬ ኮስቼርስ ሞተርስ ቢዝነስ በስሩ ብዙ ቢዝነሶችን አካቷል፡፡ በናይጄሪያ ብቸኛው የቢኤምደብሊው (BMW) መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፤በ 5000 ሄክታር ላይ ያለ የሩዝ እርሻ፤ ብቸኛው የሮል ሮይስ፤ ፎርድ፤ ጃጉዋር እና ሬንጅ ሮቨር አስመጪ እና አከፋፈይ እና የተለያዩ ፔትሮኬሚካሎች አምራች ድርጅት ነው፡፡የድርጅቱ ሃብትም ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ ይገመታል፡፡
ኮስሞስ ለስኬቱ እንደ ዋና ምክንያት የሚያየው ከጃፓናውያን ጋር የነበረውን ቅርርብ፡፡ “ከጃፓናውያን ጋር በነበረኝ ቅርርብ ምክንያት ለስራ ፍቅር እንዲኖረኝ ሆኛለሁ፡፡ ለቃል መገዛትን፤ የደንበኞችን ፍላጎት ማክበርን፤ ገንዘብን በጥንቃቄ መያዝን እና ጠንክሮ መስራትን ከነሱ ነው የተማርኩት” ብሏል፡፡ኮስሞስ በተለያዩ መድረኮች እየተገኘ አነቃቂ ንግሮችን በማድረግ እና ለናይጄሪያ ወጣቶች የራሱን የህይወት ልምዶች በማካፈል ለስራ የሚያነሳሳ ሰው ነው፡፡
ኮስሞስ ከሰጣቸው የቢዝነስ ምክሮች ውስጥም
1. ቢዝነስ ለመስራት የሚያስፈልገው ካፒታል ብቻ አይደለም፡፡ ልትሰሩ ወይም ልትገቡ የምትፈልጉበትን ቢዝነስ ማወቅ ነው መጀመሪያ የሚያስፈልገው፡፡ የገንዘብ አስፈላጊነት 40 በመቶ ያህል ነው፡፡ ዋናው ስለቢዝነስ ብቻ ሳይሆን ልትሰሩ ስላሰባችሁት ቢዝነስ እና ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ያላችሁ እውቀት ነው ይላል፡፡
2. ለራሳችሁ እና ለስራችሁ ጥርት ያለ ራእይ ከሌላችሁ ችግር እና ኪሳራ በቀላሉ ይበግራችሁዋል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ራእይ ይኑራችሁ፡፡ ልትደርሱበት የምትፈልጉበትን ነገር ጠንቅቃችሁ እወቁ ብሎ ኮስሞስ ይመክራል፡፡